ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች የሚከሰቱ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመፍታት በጥናትና በሀገር በቀል እውቀት ላይ የተመሰረተ መፍትሄ ያስፈልጋል ተባለ (ግንቦት 06 ቀን 2014ዓ/ም አዲስ አበባ): መቀመጫውን በእንግሊዝ ያደረገውና በትውልደ ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ደስታ ሄሊሶ መስራችነት የተቋቋመው ሶፎስ /ጥበብ/ መንግስታዊ ያልሆነ የጥናትና ምርምር ድርጅት በይፋ ስራውን ጀምሯል፡፡ ለንደን በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በተካሄደ ስነስርአት ላይ በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተፈሪ መለሰ እንደተናገሩት ሶፎስ አፍሪካ መቀመጫውን ኢትዮጵያ በማድረግ ተመሳሳይ ተግባራት በአፍሪካ ሀገሮች ላይ ጭምር እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ አክለውም በጥናት እና ሀገር በቀል አውቀት ላይ ተመስርቶ የማህበረሰብን የሞራል እሴቶች ለማጎልበት፣በሀይማኖት ፣ በግብረገብነት ፣ በትምህርት እና በምርምር ስራ ላይ ማትኮር ጤናማ ማህበረሰብን ለመገንባት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡
የሶፎስ አፍሪካ መስራች ትውልደ ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ደስታ ሄሊሶ በበኩላቸው ሶፎስ አፍሪካ ኢትዮጵያ የገጠማትን ስብራት መሰረታዊ ምንነትና መንስኤ ላይ ጥናት በማድረግ የመፍትሄ ሀሳቦችን በማመንጨት ህብረተሰቡ ለአዎንታዊ ለውጥ ዝግጁ እንዲሆን ማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡ ሶፎስ አፍሪካ አዲስ አስተሳሰብና አሰራር እሳቤን በማዳበር ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገሮችን ተብትቦ የያዘውን የሙስና ፣ የሀይማኖት አክራሪነት ፣ እንዲሁም የጎሳና የአክራሪ ብሄርተኝነት በማሰወገድ ህብረተሰቡ የጋራ እሴቶችን በመገንባት ተካብብሮና ተቻችሎ እንዲኖር ድርጅቱ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡። ግብረሰናይ ድርጅቱ በሀገር በቀል እውቀት ላይ ተመስርቶ ኢትዮጵያና ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮችን ለወረረው ድህነት ተኮር የእርስ በእርስ ግጭትና ይህን ተከትሎ ለሰፈነው ማህበራዊና ስነልቡናዊ ቀውስ መፍትሄ ለመፈለግ እንደሚሰራ ተመልክቷል፡፡ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ለአፍሪካ ሀገሮች እስከ አሁን ያደርግ የነበረው እርዳታ ለውጥ ያላመጣ በመሆኑ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ሰትራቴጂውን እንዲከልስና አዲስ አሰራር እንዲቀይስ ጥረት ያደርጋል ብለዋል፡፡ በእለቱም የኢትዮጵያን የንግድና የኢንቨስትመንት እድሎች የማስተዋወቅ ተግባር ተከናውኗል፡; በለንደን የኢትዮጰያ ኤምባሲ በተካሄደ ስነስርአት በኢትዮጵያና በዩናይትድ ኪንግደም መካከል ስላለው የህዝብ ለህዝብ ግኑኝነት ፣ በሀይማኖት ጽንፈኝነት፣የጎሳና ብሄር አክራሪነት ላይ በታዋቂ ምሁራን ዝርዝር ማብራሪያዎችተሰጥተዋል፡፡ ሶፎስ አፍሪካ ባለፈው አመት በኢትዮጵያ ስራውን ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የጥናትና ምርምር ባለሙያዎች እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት በይፋ ስራውን መጀመሩ ይታወሳል፡፡